ሰኔ 3/2000 ዓ.ም
ያረጋል የኋሌ
“ሶስት ዛፍ ለሶስት ሺ” ኘሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተመለከተ፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ዛሬ እንደገለፁት “ሶስት ዛፍ ለሶስት ሺ” የዛፍ ችግኝ ተከላ ውጤታማ እንዲሆን እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዚህ የአገር በቀል የዛፍ ችግኝ ተከላ በአዲስ አበባ አካባቢ ብቻ ከ2 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ጽ/ቤቱ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንና የተከላው ሥነ-ሥርዓት በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለተከላ የሚሆኑ ችግኞችን የአዘጋጀ በመሆኑ የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች በቡድን እየሆኑ ችግኝ የመትከል ሥራውን ማከናወን እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
ችግኞቹ በቋሚ ቅርስነት ለትውልድ ከመተላለፋቸውም በተጨማሪ የአካባቢያችንን ሥነ-ምህዳር የተስተካከለ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የገለፁት አቶ ቴዎድሮስ የከተማው ነዋሪ ይህን ተገንዝቦ ነገ ዛሬ ሳይል በችግኝ ተከላው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ባለፈው ሁለት ዛፍ ለሁለት ሺ” ኘሮጀክት ከ2-5 ሚሊየን በላይ አገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በዘንድሮው “ሶስት ዛፍ ለሶስት ሺ” ኘሮጀክትም በተከላና በእንክብካቤ ሥራው ከከተማው ነዋሪ በተጨማሪ የውጭ ዲኘሎማቶችና ኤምባሲዎችም እንደአለፈው ተከላ ሁሉ ተሳትፎአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ይህን ማድረግ ከተቻለ የመዲናችንን የአየር ሚዛን በመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸርን በመንከባከብ፣ የሀይል አቅርቦትን በማስተካከልና ተፈጥሮን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ይህንንም አርአያነት ያለው ተግባር ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ በመቁጠር ሁሉም በአንድነት ስሜት እንዲሳተፍ ነው ያስገነዘቡት፡፡
<< Back
to Home >> |