መጋቢት 2 ቀን 2000 ዓ.ም
ያረጋል የኋሌ
በአዲሱ ሚሌኒየም ሴቶች በልማት የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ነጋዴ ሴቶች ማህበር አስታወቀ፡፡
ማህበሩ ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሸ ባካሄደው የውይይት መድረክ የአዲስ አበባ ሴት ነጋዴ ሴቶች ማህበር ኘሬዝዳንት ወ/ሮ አቻምየለሽ አሸናፊ እንደገለፁት ሴቶች በንግድና ኢንቨስትመንት የሚያደርጉትን ተሳትፎ በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጠ ይኖርባቸዋል፡፡
ሴቶች ራሳቸውን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት አላቀው በማንኛውም የስራ ዘርፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማጐልበት ለአገራችን ህዳሴ እውን መሆን በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል በመሆናቸው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸው እንዲጐለብት በሚመለከታቸው አካላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
የሚሌኒየሙ የበአል አከባበር ሲጀመር ጀምሮ ሴቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኪሮስ በመንግስት አገራችን በመጭዎቹ 20 ዓመታት መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን እንገነባለን ተብሎ እራይ ሲያስቀምጥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ግምት ውስጥ በማስገባት በመሆኑ ማህበሩ ይህንን የልማት ተሳትፎ ከአመት አመት አጠናክሮ በመቀጠል የሴቶችን በተግባር እውን ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ማህበሩ ከአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ጋር ባዘጋጀው በዚህ የአንድ ቀን የውይይት መድረክ የማህበሩ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ በመሆን የሴቶች የመሪነት ሚና፣ የመደራጀት መብት ጠቀሜታና አስፈላጊነት እንዲሁም በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
<< Back
to Home >> |