የካቲት 24 ቀን 2000 ዓ.ም
ገናናው ከተማ
አዲስ አበባን የበለፀገችና ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆኗን ለማስተዋወቅ 12ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒት ጥሩ ተሞክሮ እንደነበር ተገለፀ፡፡
ከየካቲት 13-19/2000 ዓ.ም የተካሔደውን የንግድ ትርዒት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ልዩ ፖቪሊዮንን በመወከል ተሳትፎ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት የምስክር ወረቀት በተሰጠበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምክትል ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ቢፍቱ እንደገለፁት፣ አዲስ አበባን የበለፀገችና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንዲሁም መልካም ገፅታዋን ለማስተዋወቅ የንግድ ትርዒቱ ጥሩ ተሞክሮ ነበር፡፡
በተገኘው አጋጣሚ የአዲስ አበባን ታሪክ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች መሠረተ ልማቷን ለማስተዋወቅ ጥረት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ግርማ በቀጣይም በጋራ ከሰራን የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
በስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የአዲስ አበባ ፖቫሊዮን አስተባባሪ አቶ ግርማ አበበ በበኩላቸው በ12ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም ዓቀፍ ንግድ ትርዒት የአዲስ አበባ ልዩ ፖቫሊዮን ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ተስማሚ መሆኗንና ዕድገቷ ተስፋ ባለው ጎዳና ላይ መሆኑን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የዘርፍ ማህበራት ዋና ፀሐፊ አቶ ታምራት አድማሱም የአዲስ አበባ ፖቫሊዮን አፈፃፀም ያማረ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህንኑ ጥሩ ጅማሬ በማጠናከር በቀጣይም ለከተማችን ውበትና ዕድገት በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
የምስክር ወረቀት ከተሰጣቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቀጣጠሪያ ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ማስታወቂያና ባህል ቢሮ፣ ቅዱስ ሚካኤል ማተሚያ ቤት፣ ጄኔራል መርካንታይል፣ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ ኤክስትሪም ሆቴል እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ከየካቲት 13-19/2000 ዓ.ም የተካሄደውን 12ኛውን አዲስ ቻምበር ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒትን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮክቴል አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀው የእራት ግብዣና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ በርካታ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
<< Back
to Home >> |