ሰኔ 2 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
በሚሌኒየሙ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት በቅንጅት መተግበር እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
የአልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኘሬዝዳንት ኘሮፌሰር እሸቱ ወንጨቆ ሰሞኑን እንዳስታወቁት በተያዘው ሚሌኒየም ሁለተንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የሰለጠነ የሰው ኃይል በየደረጃው የማፍራቱ ጥረት በቅንጅት ሊተገበር ይገባል ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን የዕድገት አቅጣጫና ተጨባጭ ሁኔታን ያገናዘበ ስርዓት ትምህርት በመንደፍ ጥራት ያለው ስልጠና መስጠት የግልም ሆኑ የመንግስት የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ መሰረት በርቀት ትምህርት ፋና ወጊ የሆነው አልፋ ባለፉት 26 ዓመታት ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችን በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች ማስመረቁን ኘሮፌሰር እሸቱ ተናግረዋል፡፡
አሁንም በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ወገኖች በተለያዩ የትምህርት አይነቶች በምስክር ወረቀት፣ በዲኘሎማና በዲግሪ መርሀ ግብር የርቀት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የራሱን ሕንፃ በጐተራና በአራት ኪሎ አካባቢ በመገንባት የርቀት ትምህርቱንና መደበኛ ስልጠናውን በማስተባበር ላይ እንደሚገኙ ኘሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የመደበኛ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ኘሮፌሰር እሸቱ ጠቁመው በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂና በሕግ የትምህርት መስኮች ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ሰልጣኞች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተሟላ ቤተ መጽሐፍት፣ በድምጽና አይቲ ቤተ ሙከራዎች በሌሎች የትምህርት መረጃዎች በመታገዝ ትምህርት በመሰጠት ላይ መሆኑን ኘሮፌሰር እሸቱ ገልፀዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ ባሉ የማስተባበሪያና የማካካሻ ማዕከላት አማካኝነት የርቀት ትምህርቱን ጥራት በማስጠበቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ባቋቋመው ማዕከል አማካኝነትም የትምህርት ጥራት ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ በድህረ ምረቃ መርሀ ግብር ስልጠና ለመጀመር ዝግጁቱን ያጠናቀቀ መሆኑን ኘሬዝዳንቱ ይፋ አድርገዋል፡፡
የዛሬው አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከ26 ዓመታት በፊት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አልፋ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ አክሲዎን ማህበር በሚል መቋቋሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |