ሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም

ቁምላቸው አበበ

አሜን ኢትዮጵያ የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት በአዲሱ ሚሌኒየም በኢትዮጵያውያን መካከል የመግባባትና የመደማመጥ ባህል እንዲጐለበት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የአሜን ኢትዮጵያ ማህበር ኘሬዝዳንትና ምክትል አባ ጴጥሮስ በርጋና ዶ/ር ሰለሞን ንጉስ ድርጅቱ ከፍትህ ሚኒስቴር ህጋዊ እውቅና ማግኘቱን አስመልክቶ ትላንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ማህበሩ በኢትዮጵያውያን መካከል መደማመጥ፣ መግባባትና መከባበር እንዲጐለብት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡

በቅርቡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በመግባባትና በመደማመጥ ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናቶችን አሜን ኢትዮጵያ እንደሚያዘጋጅ ኘሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

የአመለካከትና የሀሳብ ልዩነትን የሚያከብር እንዲሁም ተቃውሞን የሚያስተናግድ ሆደ ሰፊ ትውልድ ለማነጽ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ዓብይ የማህበሩ ተልዕኮ መሆኑን አባ ጴጥሮስ አስገንዝበዋል፡፡

የአሜን ኢትዮጵያ ምክትል ኘሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ንጉስ በበኩላቸው ማህበሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አባላትና ደጋፊዎች እንዳሉት ገልፀው፣ የአባላቱ የሙያ የሀይማኖትና የብሔር ስብጥር ዓላማውን ለማሳካት ያግዛል የሚል ስምምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ዓላማውንና ተልዕኮውን የማስተዋወቅ ስራ ከማከናወን ጐን ለጐን የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናቶችንና ሁሉንም የክልል ከተሞች የሚያደርስ የተሰፋ ጉዞ እንደሚያካሂድ ዶ/ር ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ ከፍትሕ ሚኒስቴር ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘቱን አውስተው በቀጣይ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጊቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በውጭ ሀገር የሚኖሩ 10 ኢትዮጵያውያንና ሁለት የውጭ ዜጐች የተሳተፉበት የሰላም ጉዞ ሰሜን አሜሪካን፣ አውሮፖን፣ እስያንና አፍሪካን በየብስና በባህር ለ45 ቀናት በማካለል ከ17 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ በሚሌኒየሙ ዋዜማ አዲስ አበባ መግባታቸዉን ይታወሳል፡

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum