የካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 76 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚሌኒየሙን የትምህርት ቀን በጋራ ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገለፀ፡፡
የክፍለ ከተማው የሚሌኒየሙ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው እሸቱ ዛሬ እንዳስታወቁት ተቋማቱ በመጋቢት ወር በኤግዚቢሽን ማዕከል ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚያከብሩት በዓል በተማሪዎች የተዘጋጁ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በበዓሉ የተለያዩ ት/ቤቶች መሳተፋቸው ልምድ ለመለዋወጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፖኬጆችን የበለጠ ለማስገንዘብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለሕዝቡ ከማስተዋወቅና ገብያ ከመፍጠር አኳያም የጐላ አስተዋፆ እንደሚኖራቸው አቶ ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ጐልቶ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስና ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚሌኒየሙ የትራፊክ ሳምንት በቅርብ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡
የሴቶችን የልማት ድርሻና ተሳትፎ ለመዘከር የክፍለ ከተማውን የሴቶች የሚሌኒየም በዓል ለማክበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
በክፍለ ከተማ የሚገኙ 56 ትምህርት ቤቶች የሚሌኒየሙን የትምህርት ቀን በዓል በድምቀት ማክበራቸውን አቶ ጌታቸው አውስተዋል፡፡
በዓሉ ተማሪዎች ባህላቸውን በውል እንዲገነዘቡ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ቃል የገቡበት አጋጣሚ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
<< Back
to Home >> |