ነሐሴ 15 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የሚሌኒየሙ የመጀመሪያ የአሸንዳ በዓል የፊታችን ቅዳሜ በኤድናሞል ሲኒማ አዳራሽ በድምቀት እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ትላንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በዕለቱ የወይዘሪት አሸንዳ የቁንጅና ውድድርን ጨምሮ የባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡
ባህላዊ ኮንሰርቱ የአሸንዳን ባህላዊ አጨፋፈር ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያግዛል፡፡
የአሸንዳ በዓል በአዲስ አበባ መከበሩ ባህሉን ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ለማስተዋወቅ አስተዋፆ እንደሚኖረው ተመልክቷል፡፡
የዳዕሮ ማስታወቂያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክኤ ገ/መድህን በበኩላቸው የአሸንዳ በዓል ከጥንት ጀምሮ በትግራይ ሲከበር መቆየቱን አውስተዋል፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ ወ/ሪት ራሔል ተከስተ እንደገለፀችው በወ/ሪት አሸንዳ የቁንጅና ውድድር የታጋይ ልጆች ይሳተፋሉ፡፡
ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡት የማበረታቻ ሽልማት መዘጋጀቱንም ተናግራለች፡፡
ወ/ሮ መአዛ ኃ/ማርያም በበኩሏ በዝግጅቱ ድምፃዊት ሊታይ መስፍንን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ድምፃውያን እንደሚሳተፉ አስታውቃለች፡፡
ኮንሰርቱ በኤድናሞል ሲኒማ አዳራሽ ቅዳሜ ነሐሴ 17 ከጠዋቱ ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የመግቢያ ትኬቶች የአክሱም ሆቴልን ጨምሮ በሌሎች ታላላቅ ሆቴሎች እንደሚገኙ አስተባባሪዎቹ ገልፀዋል፡፡
በትግራይ አሸንዳ፣ በዋግ ሻደይ እየተባለ በየአመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ የሚከበር ጥንታዊ የልጃገረዶተ የጭፈራ ትርዒት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በዋግ ክምራ ዞን ዋና ከተማ ሰቆጣ በድምቀት እንደሚከበር መገለፁ ይታወሳል፡፡
<< Back
to Home >> |