መጋቢት 29 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የሕፃናትን ዝንባሌና ተሰጥኦ ለመለየትና ስለመብቶቻቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለማጐልበት የሚያግዙ የኪነ-ጥበብ ውድድሮች በቋሚነት ሊካሄዱ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃይለስላሴ ትላንት የሚሌኒየሙን የሕፃናትና የቤተሰብ ሳምንት አስመልክቶ በሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል በተዘጋጀ የስዕልና የስነ-ፅሑፍ ውድድር የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ሕፃናት መብቶቻቸውን እንዲገነዘቡና ዝንባሌዎቻቸውን እንዲለዩ ተከታታይነት ያላቸውና አሳታፊ ፌስቲቫሎች ሊዘጋጁ ይገባል፡፡
በሚሌኒየሙ 2 ሺህ ሕፃናትና ወጣቶች ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በሕፃናት መብቶች አከባበርና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽን ባለሙያና የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ታምራት ገረመው በበኩላቸው ከመጋቢት 22 ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት“መልካም ቤተሰብ ለህፃናት ዕድገትና ደህንነት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው የሚሌኒየሙ የሕፃናትና የቤተሰብ ሳምንት በሕፃናት መብት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋርውይይት መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡
ሕፃናት፣ የምክር ቤት አባላትና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተሳተፈበት ምክክር በፖርላማ አዳራሽ መካሄዱንም የዝግጅቱ አስተባባሪ አስታውቀዋል፡፡
ወላጆቻቸውን ያጡና ችግረኛ ሕፃናትን የሚያሳድጉ ተቋማት የስራ እንቅስቃሴ በዚሁ ጊዜ መጐብኘቱን አቶ ታምራት አክለው ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤትና፣ በህፃናት ዙሪያ የሚሰሩ መንግሰታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባዘጋጁት የሚሌኒየሙ የሕፃናትና የቤተሰብ ሳምንት በተዘጋጀው የስነ-ፅሑፍና የስዕል ውድድር 600 ሕፃናት መሳተፋቸውን አቶ ታምራት ገልፀዋል፡፡
በፑሽኪን አዳራሽ ለተሳታፊዎችና ለአሸናፊ ሕፃናት የምስክር ወረቀትና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶችም ቀርበዋል፡፡
<< Back
to Home >> |