መጋ 08 ቀን 2000 ዓ.ም


ቁምላቸው አበበ

በሚሌኒየሙ በአራዳ ክፍለ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኰሌጆችን ትምህርት ጥራት ለማሻሻል ትኩረት መስጠቱ ተመለከተ፡፡

የክፍለ ከተማው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቡድን መሪ መድህን ገ/ዮሐንስ ትላንት እንዳስታወቁት የኮሌጆችን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከሚደረገው ሱፐርቪዥንና ክትትል ጐን ለጐን የጥራት ማሻሻያ ፖኬጆችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው፡፡

በየደረጃው ያሉ አስፈፃሚ አካላት ስለትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፖኬጆች የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠና መስጠቱ ቡድን መሪዋ ጠቁመው በቀጣይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡

ኮሌጆች የትምህርት ጥራትና ማሻሻያ ፖኬጆችን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ አሁን ካለው የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ስለሚያስችለው ትኩረት ተሰጥቶት በመስራት ላይ መሆኑን ወ/ሮ መድህን ተናገረዋል፡፡

ለኮሌጆች ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊትና በኋላ በየሳምንቱና በየወሩ የሱፕርቪዥን ስራ በመከናወን ላይ በመሆኑ የትምህርት ጥራቱ በመሻሻል ላይ መሆኑን የቡድን መሪዋ ገልፀዋል፡፡

በየሁለት አመቱ እየተገመገሙ ደረጃቸውን በትክክል ጠብቀው ሲገኙ የዕውቅና ፈቃዱ እንደሚታደስ ወ/ሮ መድህን ጠቁመው ደረጃቸውን ላልጠበቁት ደግሞ የምክርና የድጋፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስተውቀዋል፡፡

መስፈርቱን ማሟላት ባልቻሉ ኮሌጆች ላይ ግን በየደረጃው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ወ/ሮ መድህን አስገንዝበዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ 80 የቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ትምህርት ተቋማት ሲኖሩ ከ16 ሺህ 400 በላይ ሰልጣኞች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum