መጋቢት 3 ቀን 2000 ዓ.ም
ማርታ እንድርያስ
በሚሌኒየሙ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ወጣቶች የራሳቸውን ማንነት ሊያሳውቋቸው የሚችሉ መድረኮችን በስፋት ማዘጋጀት እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ማህበረ ቅዱሳን ከየካቲት 23 ቀን ጀምሮ በኤግዚቢሽን ማዕከል ለህዝብ ክፍት ያደረገውን አውደ ርዕይ በመስመልከት የማህበሩ ሰብሳቢ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም እንደተናገሩት በሚሌኒየሙ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ወጣቶች ማነነታቸውን ሊያሳውቃቸው የሚችሉ መድረኮችን በስፋት ማዘጋጀት ይገባል፡፡
ዲ/ን ሙሉጌታ ማህበሩ ይህንን ጥረት ለማገዝ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት ሲያብራሩም ማህበረ ቅዱሳን ከሚሌኒየሙ መባቻ ጀምሮ ትውልዱን በትምህርት የማነፅ አቅም ያላቸው የተለያዩ አውደ ጥናቶችንና አውደ ርዕዮችን በስፋት በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመው ይህ አውደ ርዕይም የዚህ አንድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአውደ ርዕዩ አስተባባሪ ዲ/ን ኤፍሬም ውበት በበኩሉ አውደ ርዕዩ በዘጠኝ አበይት ክፍሎች መከፈሉን ገልፆ በውስጡም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በሀገር እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያበረከተቻቸውን አስተዋፅኦችና በቀጣይ ዘመናትም ሰላምን፣ ልማትንና መልካም አስተዳደርን በተሟላ መልኩ ለማስገኘት ማከናወን ስለሚገባት ተግባራት የሚዳስሱ ክፍሎችን ማካተቱን ተናግሯል፡፡
ከአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች መካከል ወጣት ኩራባቸው ደሳለኝና ወ/ሮ በስዋምየለሽ ደምሴ በሰጡን አስተያየት አወደ ርዕዩ ማህበረሰቡ ማንነቱን እንዲረዳ የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው ይህን መሰል ዝግጅት በቋሚነት ማዘጋጀት ይገባል ብለዋል፡፡
#መጪው ዘመን እንዳይቀድመን እንነሳ$ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ይህ አውደ ርዕይ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጎብኚዎች እየተመለከቱት እንደሚገኙና የዕይታ ጊዜው እንዲራዘም ከጎብኚዎች በቀረበ ጥያቄ መሰረት እስከ መጋቢት 7 ክፍት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |