ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም

ቁምላቸው አበበ

በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ቅድመ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤትና አያት አክሲዎን ማህበር የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልን አስመልክቶ ትላንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተመለከተው ከፊታችን ግንቦት 25 እስክ 30 ለሚከበረው በዓል የግንዛቤ ማስጨበጥ የሰንደቅ አላማ ህትመት፣ የብሔራዊ መዝሙር ሲዲ ዝግጅትና ሌሎች ተግባራት በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት 90 በመቶ ተጠናቀዋል፡፡

የተለያዩ መጠን ያላቸው ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰንደቅ ዓላማዎች ምርት የተጠናቀቀ ሲሆን ከአባት አርበኞች፣ ከፖሊስ፣ ከርዕሳነ መምህራን፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሉች ጋር ስለሰንደቅ ዓላማ ቀን ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸው ተመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ እንደተናገሩት የበዓሉን ዝግጅት አጠቃላይ ወጭ የአያት አክሲዮን ማህበር መስራችና ባለድርሻ አቶ አያሌው ተሰማ ሸፍነዋል፡፡

ባለሀብቱ ወደፊት በየአመቱ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ወጭ ለመሸፈን ከወዲሁ ቃል መግባታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

የበዓሉን ወጭ የአያት አክሲዎን ማህበር መስራችና ባለድርሻ አቶ አያሌው ተሰማ በበኩላቸው የማንነቴ መገለጫ የሆነውን ሰንደቀ አላማ ለማክበር ተሳታፊ መሆን መቻሌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል፡፡

ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ክብር እልፍ አእላፍ ሕይወታቸውን ቤዛ እያደረጉ ባሉበት ወቅት ካፈራሁት ሀብት ቆርሼ ለዚህ ታላቀ ተግባር ማዋሌ የዜግነት ግዴታዬ ከመሆኑ ባሻገር ወደፊትም ከምንም በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ይህን በዓል በየአመቱ ስፖንሰር የማድረግ ፍላጐት እንዳላቸው አቶ አያሌው ጠቁመው የመጀመሪያ ለሆነው የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል ከሶስት እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ወጭ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩተ በሚሌኒየም የመጀመሪያ የሆነው የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አስተዋፆ ከማድረጉ ባሻገር ስለ ባንዲራ ፍቅርና ክብር ያለው ትውልድ ለመቅረጽ ያግዛል፡፡

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum