ሰኔ 28/2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ

 

በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው የሚሌኒየሙ የኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በብሔራዊ ስታዲዮም በድምቀት ተከበረ፡፡

የኢፌድሪ ኘሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሁለቱም ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ሚኒስትሮች አምባሳደሮች እንዲሁም የሀይማኖት መሪዎችና ከ30 ሺህ በላይ የመዲናዋ ነዋሪዎች በብሔራዊ ስታዲዮም ታድመውበታል፡፡

ኘሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የማንነታችን መገለጫ የሆነው የሰንደቅ ዓላማችን ክብር እንዲጐላ ዜጐች ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማችንን በክብር ጠብቀው ያቆዩትን ጀግኖች አርበኞች ሰማዕታትና ታጋዮች በዚህ ታሪካዊ ዕለት ሊዘከሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሚሌኒየሙ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለሰንደቅ አላማችን ያለንን  ታማኝነት የምንገልጽበት ዕለት ከመሆኑ ባሻገር ለሀገራችን ህዳሴ ያለንን ቁርጠኝነት የምናሳይበት አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ደግፌ ቡላም ሰንደቅ ዓላማችንም ሆነ ብሔራዊ መዝሙራችን የብሔር ብሐረሰቦችንና የሀይማኖቶችን እኩልነት የሚያፀባርቅ በመሆኑ ቀደም ሲል ከነበሩት ሰንደቅ ዓላማዎች ይለያል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበኩላቸው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓሉን በየአመቱ ለማክበር የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ፀድቆ በሚቀጥለው አመት ስራ ላይ እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚሌኒየም አከባበር ም/ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ስዩም መስፍን በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንተናገሩት ኋላ ቀርነትን ጠንክሮ በመሥራት ማሸነፍና አስተማማኘ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ለሰንደቅ ዓላማችን ክብር መስጠት ነው ብለዋል፡፡

ለበዓሉ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለድርሻ አካላትን በተለይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰንደቅ ዓላማችን በማዘጋጀትና የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ድጋፍ ያደረጉትን የአያት አክሲዮን ማህበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርን አቶ አያሌው ተሰማን አመስግነዋል፡፡

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በክብር ዘብ ታጅበው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ተረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ኘሬዝዳንት ሊቀ ትጉአን አስታጥቄ አባተና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘጠኙን ክልሎች ለሚወክሉ አገር ተረካቢ ወጣቶች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአደራ አስረክበዋል፡፡

በኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት በአቶ ከማል በድሪ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን ትርጉምና መሪ ሐሳብ አስመልክቶ የቃለ መሀላ ስነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በሚሌኒየሙ የመጀመሪያ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት፣ ብሔራዊ የሚሌኒየም አከባበር ምክር ቤትና አያት አክሲዮን ማህበር በጋራ እንዳዘጋጁት ቀደም ሲል መገለፁ ይታወሳል፡

 

 

 

 

<< Back to Home >>

 
 
Ethiopian National Flag Day

የሚሌኒየሙ የኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በብሔራዊ ስታዲዮም ሲከበር፡፡

 
Addis Millennium Bottum