ሰኔ 17/2000 ዓ.ም
ገናናው ከተማ
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአዲሱ ሚሌኒየም በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን መነሳሳትና ብሔራዊ መግባባት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተገለፀ፡፡
የፊታችን ሰኔ 28 የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ብሔራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም በረደድ እንደገለፁት፣ የሰንደቅ አላማ ቀን በአዲሱ ሚሌኒየም በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን መነሳሳትና ብሔራዊ መግባባት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው፡፡
እንደ አቶ ስዩም ገለጻ፣ በሚሌኒየሙ የተፈጠረውን የመነቃቃት መንፈስ ወደ ላቀ ደረጃ በማሻገር መላው ህዝባችን ድህነትን ተረት በማድረግ የኢትዮጵያ ህዳሴን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ የሚቻለው ሁላችንም በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንሰራ ብቻ ነው፡፡
በማዕከላዊነት ለሚከበረው የሚሌኒየሙ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የዝግጅት ቦታ የታሰበው በብሔራዊ ስቴዲየም መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዕለቱም ሰንደቅ ዓላማ የመስቀልና የህዝብ መዝሙር በህብረት የመዘመር ስነ-ስርዓት እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የጥንታዊ አርበኞች፣ የስካውቶችና የወጣቶች እንዲሁም ወታደራዊ ትዕይንቶችና ሰልፎች እንደሚቀርቡ አቶ ስዩም ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ በተደረገው ውይይትም የሰንደቅ ዓላማ ቀን ከመከበሩ በፊት ዓላማውን በስፋት ማስተዋወቅና ግንዛቤ ማስረጽ እንደሚገባ ተመልክቷል፣፣
በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር እንዲቻልም ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡
<< Back
to Home >> |