ሚያዚያ 4 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር ቀን ከግንቦት ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
በአቶ ተፈሪ የማነ ሀሳብ አመንጭነትና በአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ቀን አከባበር የመነሻ ሀሳብ ውይይት በመስተዳደሩ ካቢኔ አዳራሽ ዛሬ ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን የመሩት ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የሕዝብ መዝሙር ብሔራዊ መግባባትን ለማጐልበትና የጋራ አገራዊ አመለካከት ለመጨበጥ የላቀ አስተዋፆ እንዳላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራዊ ክብራችንንና አንድነታችንን የሚፈታተነውን ድህነት በማስወገድና የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅፋቶችን በጋራ በመመከት የሰንደቅ አላማችንን ክብር ማስጠበቅ እንደሚገባ ክቡር ስዩም መስፍን አመልክተዋል፡፡
የማስታወቂያ ሚኒስትር ብርሀነ ሀይሉ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአንድነትና በመፈቃቀድ የሚኖሩባት ሀገር መለያ የሆነውን ባንዲራና ሕዝብ መዝሙር በማስተዋወቅ ረገድ ቀደም ሲል ብዙ እንዳልተሠራበት ጠቁመው፣ በሚሌኒየሙ ሀሳቡ መነሳቱ ግን የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ሚሌኒየም አከባበር ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም በረደድ በበኩላቸው በተለይ ወጣቱ የኢትዮጵያን ባንዲራና የህዝብ መዝሙር በውል እንዲገነዘብ የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጊዜአዊ ባለአደራ አስተዳደር የማስታወቂያና ባህል ቢሮ ኃላፊ አቶ ምስጋኑ አርጋ የሰንደቅ አላማ ቀኑን አላማ ባብራሩበት ወቅት እንደገለፁት፣ በዓሉ በሚሌኒየሙ የተፈጠረውን ብሔራዊ መግባባት ቀጣይ ለማድረግ የላቀ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት የአጠቃላይ ዝግጅቶች፣ ውድድሮችና ትዕይንቶች መምሪያ ኃላፊና የሀሳቡ አመንጪ አቶ ተፈሪ የማነ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ለባንዲራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር በመጠቀም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረትም ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚያነሳሳ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ቀንን ለማክበር የሚያስፈልገውን ሙሉ ውጪ ለመሸፈን ቃል የገቡት የአያት አክሲዮን ማህበር ባለቤት አቶ አያሌው ተሰማ በዚሁ ጊዜ በሰጡት አስተያየት የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ቀን ለማክበር አስተዋፅኦ ማድረግ የዜግነት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይነት የሚዘጋጅ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ባዓላትንም ለመደገፍ ባለሀብቱ ቃል የገቡ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የባለሀብቱ ተነሳሽነትና አስተዋፅ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ስም አመስግነዋል፡፡
አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን በመሰረታዊነት የያዘው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር በዓሉን አስመልክቶ ከተዘጋጀው ጽሁፍ ለማስረዳት ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |