ግንቦት 28 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ማሻሻያና አርማ ረቂቅ አወጅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑ ተመለከተ፡፡
አዋጁ በሚቀጥለው የበጀት አመት ፀድቆ ስራ ላይ ሲውል የተዘበራረቀውን የሰንደቅ አላማ አጠቃቀም ወጭ ለማድረግ እንደሚያስችልም ተገልጿል፡፡
በኢ.ፌ.ድሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የማስታወቂያ ቋሚ ኰሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዳዊት ተፈራ ትላንት በሸራተን አዲስ የሚሌኒየሙን የሰንደቅ አላማ ቀን ለማክበር በተዘጋጀ ውይይት ላይ እንደተናገሩት በኢፌድሪ ሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ ሰንደቅ አላማ የሚሰቀለበትና የሚወርድበት ሰዓት በግልፅ ቢደነገግም አብዛኛውን ጊዜ ተግባራዊ ሲሆን አይስተዋልም፡፡
በመጭው የበጀት አመት በምክር ቤቱ ፅድቆ ስራ ላይ የሚውለው የሰንደቅ አላማና የአርማ አጠቃቀም አዋጅ አሁን የሚታየውን የተደነጋገረና የተዘበራረቀ አጠቃቀም ያስተካክላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተከበሩ አቶ ዳዊት አስታውቀዋል፡፡
ብሔራዊ ሰንደቅ አላማው መሀሉ ላይ አርማ እንዳለው በዚሁ አዋጅ ላይ በግልፅ ቢቀመጥም በአግባቡ ጥቅም ላይ ካለመዋሉ ባሻገር በአብዛኛው አርማ የሌለው ሰንደቅ ዓላማ ሲውልበለብ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን እየታየ ያለው ችግር በአዋጅ ያለው ችግር በአዋጅ ብቻ የሚቃለል አለመሆኑን አስገንዝበው ሕዝቡ ስለ ኢፌድሪ ሰንደቅ አላማና መዝሙር ግንዛቤ እንዲኖረው ተከታታይነት ያለው የማስተዋወቅ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ኘሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ታሪካዊ ጉዞ ባስቃኘው ጥናታዊ ፅሑፋቸው ቀደም ሲል የነበሩት መንግስታትና ነገስታት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተለያየ አርማና ቅርፅ ያላቸውን ሰንደቅ አላማዎች ይጠቀሙ እንደነበር አውስተዋል፡፡
አያይዘው በሰንደቅ አላማችን የሀገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ሕዝብን እንዳነሳሳንበት ሁሉ ሀገራችንን ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ በምናደርገው ርብርብም ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል፡፡
ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል በአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት የአጠቃላይ ዝግጅቶች፣ ትዕይንቶችና ውድድሮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራ ገረመው የሰንደቅ አላማንና አርማ አጠቃቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ ለማድረግ ከሚዘጋጀው የሕግ ማዕቀብ ጐን ሕዝቡን በባለቤትነት ያሳተፉ የማስተዋወቅ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላው የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ ወ/ሮ ቤተልሄም አያሌው በበኩሏ ቤተሰብ ልጆቹን ስለሀገር ፍቅርና ስለባንዲራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከህፃንነታቸው ጀምሮ የማስተማር ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝባለች፡፡
የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን የሚያንፁ ትምህርት ቤቶችም የሰንደቅ አላማንና የብሔራዊ ሕዝብ መዝሙሩን ትርጉም የማስረፅ ታላቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁማለች፡፡
<< Back
to Home >> |