ግንቦት 27 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
በሚሌኒየሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአንድነት ድህነትንና ኋላቀርነትን ድል አድርገን በክብር ለማውለብለብ ቃል የምንገባበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ አስታወቁ፡፡
የሚሌኒየሙ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሸራተን አዲስ በተካሄደ ውይይት ላይ የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንደተናገሩት የሰንደቅ አላማ ቀን የዜግነትና የሰንደቅ አላማችን ክብር አደጋ የሆኑትን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ ወሳኝ የሆነውን ሀገራዊ መግባባት የበለጠ ያጐለብታል ብለዋል፡፡
የአሁኑ ትውልድ የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ፍቅር በውል ተገንዝቦ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለሰላምና ድህነትን ለማንበርከክ ሊያውለው እንደሚገባ የተከበሩ አምባሳደር ተሾመ አስገንዝበዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዜጐች ሰንደቅ አላማን እያውለበለቡ ለሀገራቸው ልማትና ብሔራዊ ደህንነት ቃል ኪዳናቸውን በየዓመቱ የሚያድሱበት ቋሚ ዕለት እንዲኖር የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሚሌኒየሙ የመጀመሪያ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ያዘጋጁትን የአዲስ አበባና የብሔራዊ ሚሌኒየም ም/ቤት እንዲሁም የበዓሉን ሙሉ ወጭ የሸፈኑትን የአያት አክሲዮን ማህበር መስራችና ባለድርሻ አቶ አያሌው ተሰማን አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በዓል አከባበር ብሔራዊ ም/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም በረደድ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የሰንደቅ አላማና የብሔራዊ መዝሙር ቀን ብሔራዊ መግባባትን በማጐልበት ሕዝቦችን በአንድነት ለልማት ለማነሳሳት ያግዛል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው የሰንደቅ አላማና የብሔራዊ መዝሙር ቀን ታሪካዊ በዓል ተሳታፊ መሆኔ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል ሲሉ የበዓሉን ሙሉ ወጭ የሸፈነው የአያት አክሲዮን ማህበር መስራችና ባለቤት አቶ አያሌው ተሰማ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በየአመቱ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ወጭ በሕይወት እስካለሁ ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን ቃል እገባለሁ ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው በቀኝ ገዥዎችና በተስፋፊዎች ዘመን እንኳ የኢትዮጵያ ባንዲራ ክብር ተጠብቆ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
ካለፉት 50 አመታት ወዲህም በጀግኖች አትሌቶቻችን አንፀባራቂ ድል የተነሳ ሰንደቅ አላማችን ከአፅናፍ አፅናፍ በክብር መውለብለቡንና ብሔራዊ መዝሙሩም ከፍ ብሎ መዘመሩን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ኘሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ ጉዞ ቅኝት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ የሰንደቅ አላማውን ታሪካዊና ትርጉማዊ አንድምታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሰንደቅ አላማን የሀገርን ኃያልነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ሕዝባዊ ንቅናቄን ለማቀጣጠል እንደተጠቀምንበት ሁሉ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመታገልም ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የማስታወቂያ ቋሚ ኰሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ዳዊት ተፈራና ምክትል ሰብሳቢው የተከበሩ አቶ አህመድ ሀሰን በጋራ “ሰንደቅ ዓላማና ሕገ መንግስታዊ መሰረቱ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡
<< Back
to Home >> |