የካቲት 28 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የሚሌኒየሙን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በመዲናችን የእግር ጉዞ ተካሄደ፡፡
#ጄንደር ቤዝድ ቫዮለንስ ካምፔይን$ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትና የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት በመተባበር የተዘጋጀው የእግር ጉዞ መነሻው አራት ኪሎ ሲሆን መድረሻው ደግሞ መስቀል አደባባይ ነበር፡፡
#ስኬቶቻችንን እናክብር$ በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የእግር ጉዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተካፍለዋል፡፡
የእግር ጉዞው አስተባባሪ ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር በጉዞው ማጠናቀቂያ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ለሀገሪቱ ዕድገት ሴቶች ዛሬ የሚያበረክቱትን አስተዋፅ ማድነቅና ተገቢውን ቦታ መስጠት ለነገው ውጤት ማማር መሰረት መጣል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃይለስላሴ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን የመከላከሉ ኃላፊነት ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀገራችን ለ32ኛ ጊዜ ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች በመላው ሀገሪቱ አንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል በመስቀል አደባባይ «ያለ ዕድሜ ጋብቻ ይቁም» በሚል መሪ ቃል ላይ በመመርኮዝ 30 ሰዓሊያን በአንድ ሸራ የሚያዘጋጁት ስዕል በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተመለከተ፡፡
የሰዓሊያኑ አስተባባሪ አርቲስት ዳዊት ገረሱ ዛሬ እንዳስታወቀው 100 ሜትር ርዝመትና አንድ ሜትር ስፋት ባለው ሸራ ላይ የሚሳሉ ስዕሎች እስከ ነገ አምስት ሰዓት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከነገ ጀምሮ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት እንደሚሆን አስተባባሪው አስታውቆ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለፊርማ በተዘጋጀው አቡጀዲ ላይ ፊርማቸውን በማስቀመጥ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲቆም ቃል የሚገቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግሯል፡፡
<< Back
to Home >> |