ሐምሌ 22 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የሜታ አቦ ቢራ አክሲዎን ማህበር ሰራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች በሞግሌ ተራራ 10 ሺህ አገር በቀል የዛፍ ችግኞችን ተከሉ፡፡
የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዎን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ከበደ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በ3 ችግኝ ለ3000 የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር 5 ሺህ ሰራተኞችና የአካባቢ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የችግኝ ተከላው የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅ ከማገዙ ባሻገር ለፋብሪካው በግብዓትነት የሚያገለግለውን ምንጭ የበለጠ ለማጐልበት እንደሚያግዝ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በ2 ዛፍ ለ2000 የችግኝ ተከላ ፋብሪካው ከ5 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን መትከሉን አቶ ሰለሞን አስታውሰው በቀጣይ ፋብሪካው ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሳተፍ አረጋግጠዋል፡፡
ዘንድሮም ሆነ አምና በፋብሪካው ሰራተኞችና በአካባቢው ነዋሪዎች የተተከሉ ችግኞች አድገው ዛፍ እስኪሆኑ ድረስ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
የፋብሪካው ሰራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ከፋብሪካው ከአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዳገታማ ቦታ ዝናብ ሳይበግራቸው በእግር በመጓዝ በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው በአርያነት እንደሚያስጠቅሳቸው አቶ ሰለሞን ገልፀዋል፡፡
ሞግሌ ተራራ የሜታ አቦ ቢራ የሚጠመቅበት የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ የሚፈልቅበት ቦታ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በ1959 ዓ.ም በሰበታ ከተማ የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡
<< Back
to Home >> |