መጋ 17 ቀን 2000 ዓ.ም

ቁምላቸው አበበ

 

በሚሌኒየሙ የመገናኛ ብዙሃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲበረታታ ሕዝቡን የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳደር ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ምስጋኑ አርጋ የሜሪ ጆይ ተራድኦ ድርጅትና የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት በጋራ #ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን$ በሚል ርዕስ በመስተዳደሩ አዳራሽ ዛሬ ባዘጋጅት ውይይት ላይ እንደተናገሩት በኤች. አይ. ቪ ኤድስና በሌሎች ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ከባህላቸው፣ ከሀገራቸውና ከወገናቸው ሳይርቁ እንዲያድጉ ኢትዮጵያውያን በጉዲፈቻ በስፋት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሀገር ውስጥ የጉዲፈቻ ባህል እንዲጐለብት አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ሕዝቡን የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሜሪ ጆይ ተራድኦ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ወላጅ አልባ ሕፃናትንና ችግረኛ አረጋውያን በመደገፍ ረገድ በስፋት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የግል ድርጅቶች በርካታ ሕፃናትን በጉዲፈቻ ለማሳደግ በመረባረብ ላይ መሆናቸውን ገልፀው፣ ከችግሩ ስፋት አንፃር የበለጠ የወገን ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

አስር ችግረኛ ሕፃናትን ካለፈው አንድ አመት ጀምሮ በማሳደግና በመንከባከብ ላይ ያሉት የአፍሪካ ኢኒሽቲቭ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግረኛ ሕፃናትን በመታደግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋፆ እንዲያደርግና #ይቻላል$ በሚል መርህ በአንድነት እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡

የኮልፌ ቀራኒዮ የሕፃናት ፖርላማ ሰብሳቢ ሕፃን ልቢያ አደም በበኩሏ የሕፃናት የመኖር ዋስትና የሚረጋገጠው ኢትዮጵያዊ ወገኖች በሚያደርጉት እገዛ መሆኑን አስገንዝባ፣ አንድ ሰው አንድ ችግረኛ ሕፃን እንዲያሳድግ ጥሪ አቅርባለች፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃይለስላሴ በበኩላቸው በሚሌኒየሙ ኢትዮጵያውያን ችግረኛ ሕፃናትንና አረጋውያን አቅም በፈቀደ በመርዳት ግንባር ቀደም ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች የተሳተፉ ሲሆን #ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን$ የሚለው መርህ ለማስረፅ የበኩላቸውን አስተዋፆ እንደሚያደርጉ ቃል ከመግባታቸው ባሻገር ከውጭ እርዳታ የመጠበቁን አባዜ በመከላከል ለሀገሪቱ መልካም ገፅታ ግንባታ አስተዋፆ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum