መጋ 04 ቀን 2000 ዓ.ም


ያረጋል የኋሌ

“በአዲሱ ሚሌኒየም ት/ቤቶች የስፖርተኞ መፍለቂያ ይሆናሉ በሚል መሪ ቃል ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡

አዘጋጆቹ የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት በዚህ የት/ቤቶች ውድድር ከ2500 እስከ 3000 የሚደርሱ ስፖርተኞች ይሳተፋሉ፡፡

በተለይ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ እንዳሉት ውድድሩ የአንደኛ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በስድስት የስፖርት አይነቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ለውድድር የቀረቡት የስፖርት አይነቶች በሁሉም ፆታ እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ጠረጴዛ ኳስ፣ መረብ ኳስና አትሌቲክስን እንደሚያካትት የተናገሩት ኮሚሽነሩ ከፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 6 እስከ 14/2000 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው በሚሌኒየሙ የሚካሄደው ይህ የተማሪዎች የስፖርት ውድድር በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሰረት ይጥላል ብለዋል፡፡

ይህም ተቋርጦ የነበረው የት/ቤት የስፖርት ውድድር እንዲቀጥል ከማድረጉም በተጨማሪ በስፖርቱም ዘርፍ የኢትዮጵያ ህዳሴ እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀጐስ ሀይሉ እንደገለፁትም በዚህ ስፖርታዊ ውድድር 529 የመጀመሪያ 130 የሁለተኛ ደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ውድድሩን ለማከናወንና በቀጣይም “ት/ቤቶች የስፖርተኞች መፍለቂያ ይሆናሉ” የሚለውን መሪ ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንደተፈጠረም አስረድተዋል፡፡

 

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum