የካቲት 20 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚሌኒየም የትምህርት ቀን በዓል ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በድምቀት እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
የክፍለ ከተማው የትምህርትና ስልጠና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወልዴ ዛሬ እንዳስታወቁት በንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኰሌጅ በሚከበረውና 80 ት/ቤቶች በሚሳተፉበት በዚህ በዓል በትምህርት ጥራት ላይ ያተኮረ የተለያዩ አስተማሪ ዝግጅቶች ተካተዋል፡፡
ከነገ ጀምሮ የትምህርት ቤቶችን የፈጠራ ስራ የሚያሳይ ኤግዚቢሽን ለህዝበ ክፍት እንደሚሆንና የስነ ምግባርና ሥነ-ዜጋ የአሸናፊዎች አሸናፊ የጥያቄና መልስ ውድድር እንደሚካሄድ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ሚሌኒየም የብሩህ ተስፋ ዘመን መሆኑን ለማሳየት ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት እንደሚካሄድ አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ቅዳሜ ደግሞ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ የተመረጡ አምስት የመንግስት፣ የሕዝብና የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚሸለሙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ አልባሳት፣ ሙዚቃ የሚያንፀባርቁና ሌሎች አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡም አቶ ተስፋዬ አስታውቀዋል፡፡
በክፍለ ከተማው በሚገኙ ከ80 በላይ የግል፣ የመንግስትና የሕዝብ ት/ቤቶች ከ60 ሽህ በላይ ተማሪዎች በመስተናገድ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |