የካቲት 25 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚሌኒየሙ ምርጥ ያላቸውን አምስት ትምህርት ቤቶች ሰሞኑን ዋንጫ ሸለመ፡፡
የክፍለ ከተማው የሚሌኒየሙ የትምህርት ቀን ሰሞኑን በተከበረበት ወቅት ከ80 በላይ ትምህርት ቤቶች በተሳተፉበት ውድድር ከግል ክሩዝ፣ ከመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ መጋቢት 28፣ ከመንግስት 2ኛ ደረጃ ግንቦት 20፣ ከሕዝብ የመጀመሪያ ደረጃ አዲስ አምባ፣ ከቴክኒክና ሙያ ደግሞ ከፍተኛ 20 ተቋም ተሸልሟል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለሽልማት ሊበቁ የቻሉት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጣቸውና በርካታ ተማሪዎችን ለውጤት በማብቃታቸው መሆኑን የክፍለ ከተማ ትምህርና ስልጠና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወልዴ ገልፀዋል፡፡
ሽልማቱ ትምህርት ቤቶችን ለበለጠ የትምህርት ጥራትና ውጤት እንደሚያነሳሳቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የክሩዝ ትምህርት ቤት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፉ ጐሳዬ ትምህርት ቤታቸው ለሽልማት ሊበቃ የቻለው የት/ቤቱ ማህበረሰብ በማሳተፍ በቅንጅት መስራት በመቻሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሽልማቱ የበለጠ ውጤት እንዲገኝ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፖኬጆችን ተግባራዊ ለማድረግም መሰረት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የክሩዝ ትምህርት ቤት የመሰናዶ ተማሪ ሕይወት አበበ በበኩሏ ትምህርት ቤታቸው ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠቱ ያገኘው ሽልማት ተማሪውንና ወላጆን ለተሻለ ውጤት ያነሳሳል ብላለች፡፡
የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሻምበል ስዩም ዘለቀ የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ ከወላጆች ጋር በቅርበት በመስራቱ ለውጤት እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡
<< Back
to Home >> |