ግንቦት 4 ቀን 2000 ዓ.ም


ገናናው ከተማ

የትግራይ ልማት ማህበር ባለፉት ዓመታት የትምህርትና የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ተገለፀ፡፡

የትግራይ ልማት ማህበር ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከትናንት በስቲያ በትግራይ ሆቴል ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ኘሮግራምና የእራት ግብዣ ላይ ዓለም ዓቀፍ የትግራይ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ተወልደ ገብሩ እንደገለፁት፣ ማህበሩ የትምህርትና የጤና አገልግሎትን ለማስፋፋት እያደረገ ያለው ጥረት በእጅጉ የሚበረታታ ነው፡፡

በትግራይ ባለፉት ዓመታት አንድ ሺህ ሰባት መቶ ትምህርት ቤቶች መሰራታቸውን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ የክልሉ መንግስት ለትምህርት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ የልማት ማህበሩ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ ቀደም ሲል 30 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች አሁን በአማካይ 3 ኪሎ ሜትር ብቻ ተጉዘው እንዲማሩ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ማህበሩ ጤና ጣቢያዎችንና የጤና ኬላዎችን፣ ቤተ-መጽሐፍት በመገንባት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ በርካታ ስራዎችን መስራቱን አምባሳደር ተወልደ ገብሩ አመልክተዋል፡፡

ዓለም ዓቀፍ የትግራይ ልማት ማህበር ምክትል ዳይሬክተር ኘሮፌሰር አምሃ አሰፋ በበኩላቸው በአዲሱ ሚሌኒየም የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትግል ወቅት ህይወታቸው ለተሰዋ ሰማዕታት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ በተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ ኘሮግራም ላይ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ የአዲግራት ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ የሰጠውን የ300 ካሬ ሜትር የመሬት ጨረታ ጨምሮ 250 ሺህ 250 ብር ገቢ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የትግራይ ልማት ማህበር ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ በአክሱም ሆቴል ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያና የእራት ምሽት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum