መጋ 15 ቀን 2000 ዓ.ም

ቁምላቸው አበበ

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማትና ኮሌጆች እርስ በርስ የሚያካሂዷቸው የልምድ ልውውጦች የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል አስተዋፆ ስለሚኖራቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

ሰሞኑን የአራዳ ክፍለ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማትና ኮሌጆች በኤግዚብሽን ማዕከል ባዘጋጁት አውደ ርእይ ላይ የተሳተፉ ኮሌጆች የስራ ኃላፊዎች እንደገለፁት በተለያዩ የሙያና ትምህርት ዘርፎች ስልጠና የሚሰጡ ኮሌጆች በአንድ መድረክ ላይ እንዲገኙ መደረጉ ልምድን ለመለዋወጥ ከማገዙ ባሻገር ጤናማ ውድድርን ያጐለብታል፡፡

የማይክሮሊንክ የጊዮርጊስ ካምፖስ ተባባሪ ዲን ዶ/ር ጉግሳ ማሞ ትላንት በኤግዚብሽን ማዕከል በሰጡት አስተያየት አውደ ርእዩ ኮሌጆችን ከሕዝብ ያገናኘ መድረክ መሆኑን ተናገግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የማህበረሰቡን፣ የመምህራን፣ የተማሪዎችንና ባለሀብቶችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

የቶም ቪዲዮግራፊ ማሰልጠኛ ተቋም ስራ አስኪያጅ አቶ ቶማስ ጌታቸው በበኩላቸው ከ50 በላይ ኮሌጆችና ተቋማት የተሳተፉበት አውደ ርዕይ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር መቀራረብን የፈጠረ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወደፊት መማር ለሚፈልጉትም በርካታ የስልጠና መስኮች መኖራቸውን ያስገነዘበ መሆኑን ጠቁመው፣ ኮሌጆችም በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የስልጠና ዘርፎችን ለመለየት የቻሉበት አጋጣሚ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ከመጋቢት 11 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በኤግዚብሽን ማዕከል የተዘጋጀውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችን አውደ ርዕይ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስዎች እንደተመለከቱት ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum