መጋቢት 05 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ከ70 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በሚሌኒየሙ ለሀገሪቱ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋፆ የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡
የተቋማቱ የሚሌኒየም በዓል ዝግጅት ኮሚቴ ዛሬ በማይክሮ ሊንክ ኰሌጅ በጋራ በሰጠው መግለጫ ተቋማቱ የሚሌኒየሙን ግብ ለማሳካት ስለሚኖራቸው ሚና የሚያስተዋውቅ አውደ ርዕይ ከመጋቢት 12 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በኤግዚብሽን ማዕከል ለሕዝብ ክፍት ይሆናል፡፡
ከአውደ ርዕዩ ጐን ለጐን ተቋማቱ፣ መንግስትና ቀጣሪ ድርጅቶች ምን አይነተ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልገናል በሚል ርዕይ ከፍተኛ ሙህራንና ባለስልጣናት የሚሳተፍበት ውይይት እንደሚካሄድ ኰሚቴው ጠቁሞ የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶችም እንደሚቀርቡ ገልጿል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርትና ስልጠና ጽ/ቤት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቡድን መሪ ወ/ሮ መድህን ገብረዮሐንስ እንደገለፁት አውደ ርዕዩ ተቋማቱ ከአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራትና ከብድርና ቁጠባ ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡
የተቋማቱን የፈጠራ ችሎታና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከልነት ለሕዝቡና ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ቡድን መሪዋ ተናግረዋል፡፡
የኰሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ጉግሳ ማሞ በበኩላቸው በኤግዚብሽን ማዕከል የሚዘጋጀው አውደ ርዕይና ፖናል ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያደረጉት ያለውን ጥረትና ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመለየት ያግዛል ብለዋል፡፡
የኰሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቶማስ ጌታቸውን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በተቋማት፣ በመንግስትና በቀጣሪ ድርጅቶች መካከል ያለውን የአጋርነት ግንኙነትና ለሀገር ዕድገት የሚኖራቸውን የማይተካ ሚና የማስገንዘብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በመሆኑም የአውደ ርዕዩ ዓላማ ለሕዝብ ይደርስ ዘንድ መገናኛ ብዙሃን ተከታታይነት ያለው ሽፋን እንዲሰጡ ምክትል ሰብሳቢው አሳስበው ሕዝቡም አወደ ርዕዩን በመጐብኘትና አስተያየት በመስጠት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 80 የመንግስት፣ የግልና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ16 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ከገለፃው ለመረዳት ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |