መጋ 24 ቀን 2000 ዓ.ም

ያረጋል የኋሌ

በአዲሱ ሚሌኒየም የአገራችንን መልካም ገፅታ የሚያስተዋውቁና ጠቃሚ ባህልና የሚያጐለብቱ የፊልም ስራዎች በብዛት፣ በአይነትና በጥራት ሊሰሩ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ትናንት በሚኒስቴር መሰብሰብያ አዳራሽ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የጨረቃ ለቅሶ የተሰኘው ቱውፊታዊ ፊልምን አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደር መሀሙድ ድሪር እንዳሉት በጥናት ላይ ተመሰርተው የሚዘጋጅ አገርኛ ፊልሞች በውጭው አለም የአገራችንን ባህል ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

የጨረቃ ለቅሶ የተሰኘው ፊልም መሰረቱን በባህል፣ ወግና ሥነ-ሥርዓት ላይ አድርጐ የተዘጋጀ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፊልሙ ከአገራችን አልፎ በአውሮፖና አሜሪካ ለተመልካች እይታ እንዲቀርብ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የዚህ አይነት ፊልም በአገራችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ በእንደዚህ አይነት ጥናትን መሰረት ያደረገ ባህል እና ፊልም ለመስራት ለሚያስቡ ሙያተኞች አርአያ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የጨረቃ ለቅሶ ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ያሬድ ገብረስላሴ በበኩሉ በዚህ በአዲሱ ሚሌኒየም ፊልሙን ለማዘጋጀት ከ6 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን መመልከትና ፊልሙ በተዘጋጀበት የደቡብ ውሎ ከ33 ያላነሱ አካባቢዎችን በተደጋጋሚ ማጥናት ግድ ማለቱን ተናግሯል፡፡

መሰረቱን በአማረ ክልል በደቡብ ወሎ ቱውፊታዊ ሥነ-ሥርዓትና ፍቅር ላይ ትኩረቱን ያደረገው ይህ ፊልም ተደጋጋሚ ልምምድ፣ የቀረፃና የኤዲቲንግ ስራን ጨምሮ 2 አመት ከ8 ወር ጊዜን እንደጠየቀ ገልጿል፡፡

ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ የጥሬ ገንዘብና የቁሳቁስ ወጭን ጨምሮ ከ6 መቶ 98 ሺ ብር በላይ መፍጀቱን የጠቆመው አቶ ያሬድ ፊልሙን በቅርቡ በሸራተን አዲስ በይፋ አስመርቆ በአውሮፖ፣ በአሜሪካና እስያ አገራት እየተዘዋወሩ ለማሳየት የቅድመ ዝግጅት ሥራው ከወዲሁ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

 

 

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum