መጋቢት 3 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
ሚሌኒየሙ የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚረጋገጥበትና ፈጣን የኢኰኖሚ ዕድገት የሚመዘገብበት እንደሚሆን በሀገሪቱ የሚታዩ አንዳንድ ለውጦች እንደሚያመለክቱ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /ዩኒዶ/ አንድ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ አስታወቁ፡፡
ኃላፊዋ ሚስስ አውሬሊያ ካራብሎ ትላንት በጽ/ቤታቸው አንዳስታወቁት ሀገሪቱ በተለይ ባለፉት አምስት አመታት ፈርጀ ብዙ የኢኰኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ የመሰረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታዎች ፈጣን የኢኰኖሚ ዕድገቱን ያረጋግጣሉ ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት አምስትና አስር አመታት የሀገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ የሚያመለክቱ አበረታች ልማቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ሚስስ አውሬሊያ ገልፀዋል፡፡
በተለይ የቆዳ ኢንዱሰትሪው በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ መሆኑን ጠቁመው ከጥቂት አመታት በፊት በጣት ይቆጠሩ የነበሩ የቆዳ ማለስለሻ፣ የጫማ ፋብሪካና የስፌት ተቋማት አሁን 53 መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /ዩኒዶ/ ለሀገሪቱ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት መፋጠን የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑንና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ አንደሚገኘ ሚስስ አውሬሊያ ገልፀዋል፡፡
ዩኒዶ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች በማስተዋወቅ ረገድም ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው ባለፈው ወር 26 ሀገራት የተሳተፉበት የቆዳ ምርቶች ኤግዚብሽን በሚሌኒየም አዳራሽ ማዘጋጀቱን አስታውሰዋል፡፡
ድርጅቱ የሀገሪቱን የቀርከሃ ልማት ጨምሮ ለብረታ ብረት፣ ለግብርና ኢንዱስትሪና ለሌሎች ዘርፎች ዕድገት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ሚስስ አውሬሊያ ገልፀዋል፡፡
<< Back
to Home >> |