መጋቢት 1 ቀን 2000 ዓ.ም
ገናናው ከተማ
በሚሌኒየሙ ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ሴት ተማሪዎች ፎረም ውይይት ትናንት በስብሰባ ማዕከል በተካሄደበት ወቅት የአዲስ አበባ ሴቶች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ኑሪያ የሱፍ እንደተናገሩት፣ በሚሌኒየሙ ሴቶችን በሁሉም መስክ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የትምህርትና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ ኑሪያ በሁሉም ዘርፍ ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የነገ ሀገር ተረካቢና የልማቱ አጋር የሆኑትን ሴት ተማሪዎችን በማሳተፍ ይህንን ታሪካዊ ቀን ማክበር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው በሚሌኒየሙ በሴቶች ሁለንተናዊ እኩልነትና በውይይት የሚያምን ትውልድ መፈጠር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
በቀጣይም ሴቶች በሁሉም መስክ መብታቸውን ለማስከበር የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ማህበራዊና ሲቪል ጉዳዮች ቢሮ ተወካይ አቶ መሰለ ትኩዬም ቀደም ባሉት ዓመታት የሴቶች ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት እየተነሳ ምክክርም ቢደረግም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተግባራዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሴት ተማሪዎች ፎረም ከአዲስ አበባ ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ከዩኒሴፍና ከአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በስርዓተ ፆታ እና በፆታዊ ጥቃት ላይ የተዘጋጁ ፅሑፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በዕለቱም የመንግስት ባለስልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በሺዎች የሚቆጠሩ የፎረሙ አባላት ተገኝተዋል፡፡
<< Back
to Home >> |