ነሐሴ 7 ቀን 2000 ዓ.ም

ቁምላቸው አበበ

በሚሌኒየሙ ወጣቱ የአየር ንብረት ሚዛን መዛባትን ለመከላከል የማይተካ ሚና እንዳለው ተመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤትና ወጣቶች ማህበር ትላንት በጋራ ባዘጋጁት የፖናል ውይይት ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ ምክትል ከንቲባና የማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከፍያለው አዘዘ እንዳስገነዘቡት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና የከፋ ጉዳት እያስከተለ ያለውን የአየር ንብረት መዛባት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ወጣቶች ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት የወጣቱን ማህበራዊና ኢኰኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አውስተው፣ ለፖሊሲው ተግባራዊነት ወጣቱ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው ጽ/ቤቱ በከተማዋ ፅዳትና በአካባቢ ጥበቃ ሰራዎች ወጣቱን በማሳተፉ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች የለውጥ ኃይል መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ኪሮስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም የበለጠ እንዲሳተፉ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት በሀገር በቀል ዛፎች ላይ ምርምር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ  ኘሮፌሰር ለገሰ ነጋሽ #የአየር ንብረት ለውጥና መዘዙ$ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ሀገር በቀል ዛፎችን በስፋት መትከል ይገባል፡፡

ኮንሶ፣ ግራር፣ ወይራ፣ ዝግባ፣ ዋርካና ሌሎች ሀገር በቀል ዛፎች በቀላሉ የማይደርቁና ለሀገሪቱ ስነ-ምህዳር ተስማሚ ስለሆኑ በስፋት የማባዛቱና የመትከሉ ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የውጭ ሀገር ዛፎች ተፈጥሮአዊ ዝግመተ ለውጥ ተከትለው የተባዙ ባለመሆናቸው አድገው ጥቅም ላይ ሳይውሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመድረቅ ላይ መሆናቸውን ኘሮፌሰር ለገሰ ገልፀዋል፡፡

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ለሀገር በቀል ዛፎች የበለጠ ትኩረት በመስጠት በስፋት ማባዛትና መትከል እንደሚገባ አስገንዝበው ከአመታት በፊት በናሙናነት የተተከሉ ሀገር በቀል ዛፎች የአካባቢውን የተፈጥሮ ሚዛን ማስተካከል መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማህበር ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት አበረታች ውጤት በመመዝገብ ላይ መሆኑን ኘሮፌሰር ለገሰ አስታውቀዋል፡፡

ወጣቱ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበው የሀገር በቀል ዛፎችን በመትከልና በመንከባከብ በስፋት መሳተፍ እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባና የብሔራዊ ሚሌኒየም ጽ/ቤቶች ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ትኩረት በመስጠትና ሕዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ያበረከቱት አስተዋፆ በምሳሌነት እንደሚጠቀስ ኘሮፌሰር ለገሰ ጠቁመው፣ በሚሌኒየሙ የተፈጠረው መነቃቃት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ኘሬዝዳንት ወጣት ታጠቅ ካሳ “የወጣቱ አደረጃጀት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ፅሑፍ አቅርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የዓለም የወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን የግማሽ ቀን ውይይት የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ያስተባበሩት ሲሆን ከ500 በላይ ወጣቶችም በውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum