ሚያዚያ 16 ቀን 2000 ዓ.ም
ቁምላቸው አበበ
የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የቴአትር ቤቱ 6ኛ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቶማስ ቶራ ዛሬ እንዳስታወቁት በዓሉ የአራት አስርት አመታት ጉዞውን ከሚሌኒየሙ ራዕይ ጋር በመቃኘት ይከበራል፡፡
በሚያዚያ 27 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚከበረው በዓል የባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክን ወደ ኋላ መልሰው የሚዳስሱ ዝግጅቶች በአንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
ታዋቂ ተዋንያን የተሳተፉበት የቴአትር ቀን ሌላው የዝግጅቱ አካል ሲሆን በቴአትር ቤቱና በሙያው ላይ የሚያጠነጥን ውይይት እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡
ሙዚቀኞችም ሆኑ ተዋንያኑ ካለፉት ወራት ጀምሮ ልምምድ በማድረግ ላይ እንደሆኑም አቶ ቶማስ ጠቁመዋል፡፡
ቴአትር ቤቱ ከመስተዳደሩ ቢሮዎች ጋር በአንድ ህንጻ ስር በመገኘቱና እንደሌሎች የመዲናዋ የመንግስት ቴአትር ቤቶች የራሱ ግቢና አስተዳደር የሌለው በመሆኑ የቴአትር ቤቱ አዳራሾች በተደጋጋሚ ለመስተዳድሩና ለሌሎች አካላት መሰብሰብያነት ስለሚያገለግል በስራው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረበት መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡
ላለፉት 32 ዓመታት የቴአትር ቤቱ ተዋናይና አዘጋጅ በመሆን በማገልገል ላይ ያለው አልዓዛር ሳሙኤል በበኩሉ የቴአትር ቤቱ አዳራሾች ከተቋቋሙለት ዓላማ ይልቅ በብዛት በመሰብሰብያነት በማገልገል ላይ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
አዳራሹ በስብሰባና በሌሎች ዝግጅቶች በተደጋጋሚ ስለሚያዝ የቴአትርና የሙዚቃ ልምምዶች፣ ለዕይታ የተዘጋጁ ቴአትሮችና ፊልሞች እንደሚታጠፉም ጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ከ40 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን ተፈሪ ብዙአየሁ፣ አባተ መኩሪያ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ ጌታቸው ታረቀኝና በሀይሉ መንገሻ ቀደም ባሉት አመታት የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጆች በመሆን ማገልገላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
<< Back
to Home >> |