ሰኔ 4 ቀን 2000 ዓ.ም
ያረጋል የኋሌ
በአዲሱ ሚሌኒየም ለህገወጥ ዝውውር የተጋለጡ የጐዳና ተዳዳሪና አካል ጉዳተኛ ህፃናትን ከጥቃት መከላከል የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስገነዘቡ፡፡
የአዲሰ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ የማህበራዊና ሲቪል ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የአፍሪካ የህፃናት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በአስተዳደሩ የምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በአዘጋጀው ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስንቅነሽ አዳነ እንደገለፁት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህፃናትን መንከባከብ የሁሉም ህብረተሰብ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ወደ ጐዳና የወጡት ብቻ ሳይሆን በተለያየ ችግር ምክንያት ወደ ጐዳና ለመውጣት የተዘጋጁ ህፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ጭምር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ኃ/ስላሴ በበኩላቸው የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዲሱ ሚሌኒየም ህፃናትን ከተለያዩ ጥቃቶች በመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበው ለመስራት ቃል የሚገቡበት ዕለት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ100 ሺ በላይ ህፃናት ለጐዳና ተዳዳሪነት እንደተጋለጡ ያመለከቱት አቶ ኪሮስ የችግሩን አስከፊነት በመገንዘብ በሚሌኒየሙ ለህፃናት ልዩ ትኩረት መስጠት ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የማህበራዊና ሲቪል ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ትኩዮ እንደገለፁትም ከዚህ በፊት በህፃናት እንክብካቤና ጥበቃ ላይ የሚደረጉ ጥረቶች በአዲሱ ሚሌኒየም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ለህፃናት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ካልተቻለ ተተኪ ትውልድ ለማፍራትና አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የማይቻል በመሆኑ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ በተለይም በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ህፃናትን ከጥቃት መጠበቅ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱ ከ250 በላይ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት #ህገወጥ የህፃናት ዝውውር$ በሚልና የህፃናት ጥቃት የህግ ከለላ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ይመስላል? በሚል ርዕስ በባለሙያዎች ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡
<< Back
to Home >> |