የካቲት 24 ቀን 2000 ዓ.ም


ቁምላቸው አበበ

የሚሌኒየሙን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፖኬጆችን ተግባራዊ ለማድረግ ወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ ጊዜአዊ ባለአደራ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጣሰው ሰሞኑን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚሌኒየሙ የትምህርት ቀን በተከበረበት ወቅት እንደተናገሩት የትምህርት ጥራቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የወላጆችንና የማህበረሰቡን የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡

የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ፖኬጆችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ቢሮው ዝግጅ መሆኑን አቶ ካሳሁን አረጋግጠዋል፡፡

ክፍለ ከተማው በስሩ የሚገኙ የመንግስት፣ የግልና፣ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ከትምህርት ጥራት አኳያ አወዳድሮ ምርጥ ትምህርት ቤቶችን መሸለሙ አርያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ  የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ በሚደረገው ጥረት የደከሙትን ት/በቶች ለተሻለ ውጤት የሚያነቃቃ ስለሆነ የውድድር መንፈሱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የሚካሄዱ የስነ-ምግባርና ስነ-ዜጋ ጥያቄና መልስ ውድድሮች በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋ ከማፍራትና ለትምህርት ጥራቱ መሰረት ከመጣል አኳያ የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የሚሌኒየሙን በዓል ትምህርት ቤቶች ሲያከብሩ በብሔር ብሔረሰቦች ባህል ላይ ማተኮራቸው የሀገራቸውን ባህል በውል እንዲገነዘቡ ከማስቻሉ ባሻገር የመቻቻል ባህልን እንዲለማመዱ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ ካሣሁን አስረድተዋል፡፡

 

<< Back to Home >>

 
 
 
 
Addis Millennium Bottum